የሐዲሥ ክፍል

መልስ - ከአሚረል ሙእሚኒን አቡ ሐፍስ ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ረዲየላሁ ዐንሁ በተላለፈ ሐዲሥ እንዲህ ብለዋል፡- "የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ፡- "የትኛውም ድርጊት ዋጋው ከጀርባ ባለመው እሳቤ (ኒያው) ላይ የተመሰረተ ነው። ማንኛውም ሰው የሚመነዳውም ባለመው ብቻ ነው። ለአላህና ለመልዕክተኛው ሲል የተሰደደ ሰው የተሰደደው ለአላህና ለመልእክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሆኖለታል፤ የዱንያን ጥቅም ለማግኘት ወይም ሴትን ለማጨት ብሎ የተሰደደ ሰውም እንዲሁ መሰደዱ ለተሰደደለት ጉዳይ ነው።" ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሓዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- ማንኛውም አምልኮ ሰላትም ሆነ ፆም፣ ሐጅም ይሁን ሌሎች ተግባራት ሁሉ ኒያ ሊኖራቸው የግድ ነው።
2 - ለላቀው አላህ ብሎ የሚያከናውን ሁሉ ኢኽላሱን ለአሏህ ብቻ ሊያጠራ ይገባል።
* ሁለተኛው ሐዲሥ፡

መልስ- ከምእመናን እናት ኡሙ ዐብደሏህ ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሁማ በተላለፈ ሐዲሥ እንዲህ ብላለች፦ "የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡- "በዚሁ ጉዳያችን ከእርሱ ያልሆነን አዲስ ፈሊጥ ያመጣ ይዞት የመጣው ፈሊጥ ውድቅ ነው።" ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- በሃይማኖት ውስጥ አዲስ ፈጠራ ማምጣት የተከለከለ መሆኑ።
2- አዲስ መጤ ስራዎች ተቀባይነት የሌላቸው ውድቅ መሆናቸው።
* ሦስተኛው ሐዲሥ፡

«ከእለታት አንድ ቀን የአላህ መልእክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ዘንድ ተቀምጠን ሳለን ልብሱ በጣም ነጭ ፀጉሩ በጣም ጥቁር የሆነ ሰው ብቅ አለ። የመንገደኛ ምልክትም አይታይበትም ከኛ መካከልም የሚያውቀው ሰው የለም። ወደ ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ተጠግቶ ጉልበቱን ከጉልበታቸው አስደግፎ ተቀመጠ። እጁንም ታፋው ላይ አደረገና “አንተ ሙሐመድ ሆይ! እስኪ ስለ ኢስላም ንገረኝ?” አላቸው። የአላህ መልዕክተኛም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ” ኢስላም ማለት ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ሙሐመድም የእርሱ መልዕክተኛ ናቸው ብለህ ልትመሰክር፣ ሶላት (ስርአቱን አሟልተህ) ልትሰግድ፣ ዘካን ልታወጣ፣ ረመዳንን ልትፆም፣ የጉዞውን ጣጣ ከቻልክ ደሞ ሐጅ ልታደርግ ነው።” አሉት። “እውነት ብለሃል” አላቸው። “ራሱ ጠይቆ ራሱ ‘ትክክል ነህ’ ይላቸዋል ብለን ተገረምን!”» (ከዚያም) «“ስለኢማን ንገረኝ እስኪ!” አላቸው። እርሳቸውም “በአላህ፣ በመላእክቶቹ፣ በመጽሐፍቶቹ፣ በመልእክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን ልታምንና በቀደርም ክፉውም ሆነ ደጉን ልታምን ነው።” አሉት። “እውነት ብለሃል!” አላቸው። “እስኪ ደሞ ስለ ኢሕሳን ንገረኝ!” አላቸው። እርሳቸውም “አላህን ልክ እንደምታየው ሆነህ ልታመልከው ነው፤ አንተ ባታየውም እርሱ ያይሃልና።” “ስለ ሰዓቲቱስ ንገረኝ እስኪ!” አላቸው። እርሳቸውም “ተጠያቂው ከጠያቂው የተሻለ የሚያውቀው ነገር የለም።” አሉት። “ስለምልክቶቹ ንገረኝ!” አላቸው። እሳቸውም “ሴት ባርያ ጌታዋን (አለቃዋን) መውለዷ፣ ጫማና ልብስ የሌላቸው የሆኑ እረኞች በህንፃ ሲወዳደሩ ታያለህ” አሉትና ሄደ። ከዚያም ለተወሰነ ጊዜ ቆየን የአላህ መልዕክተኛም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ዑመር ሆይ! ጠያቂው ማን እንደነበር ታውቃለህ?” አሉኝ። እኔም “አላህና መልዕክተኛው ይበልጥ ያውቃሉ” አልኩኝ። እርሳቸውም “ጂብሪል ነው! የዲናችሁን ጉዳይ ሊያስተምራችሁ መጥቶ(ነው)።” አሉኝ። ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- አምስቱ የእስልምና መሰረቶች ተወስተዋል። እነርሱም፦
“ላ ኢላሃ ኢለሏህ ሙሐመዱን ረሱሉሏህ” ብሎ በአሏህ ብቸኛ ተመላኪነትና በነብዩ ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የአሏህ መልዕክተኝነት መመስከር።
ሰላትን አሟልቶ መስገድ።
ዘካን መስጠት።
የረመዳንን ወር መፆም።
ወደ ተከበረው የአላህ ቤት ሂዶ ሐጅ ማድረግ።
2- የእምነት መሰረቶች ስድስት መሆናቸው። ስድስት ሲሆኑ እነርሱም፦
በአላህ ማመን።
በመላዕክቱ።
በመጽሐፍቱ።
በመልዕክተኞቹ።
በመጨረሻው ቀን እና
በክፉዉም በደጉም በቀደር ማመን ናቸው።
3- የኢሕሳን ምሰሶ ተወስቷል፤ እርሱም አንድ ምሰሶ ብቻ ያለው ሲሆን ይኸውም: አሏህን ልክ እንደምታየው ሆነህ ልታመልከው ነው። አንተ ባታየውም እርሱ ያይሀልና።
4- ዕለተ ትንሣኤ ጊዜው መች እንደሆነ የሚያውቀው የላቀው አላህ ብቻ መሆኑን (ተገልጿል)
አራተኛው ሐዲሥ፡

መልስ - ከአቡ ሁረይራ አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ «ከሙእሚኖች መካከል ይበልጥ ኢማናቸው የተሟላው መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸው ናቸው።» ቲርሚዚይ ዘግበውታል፤ ሐዲሡንም «ሐሰኑን ሰሒሕ" ብለውታል።
ከሐዲሡ የሚወሰዱ ቁምነገሮች፡
1- ለመልካም ስነምግባርን ማበረታታት (ማነሳሳት)
2- የስነምግባር መሟላት የኢማን መሟላት አካል መሆኑ፤
3- ኢማን የሚጨምርና የሚቀንስ መሆኑ፤
አምስተኛው ሐዲሥ፡

መልስ - ከኢብኑ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁማ በተላለፈ ሐዲሥ ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ "ከአላህ ውጪ ባለ አካል (በማንም) የማለ በእርግጥም ሽርክን ወይም ክህደትን ፈፅሟል።" ቲርሚዚይ ዘግበውታል።
ከሐዲሡ የሚወሰዱ ቁምነገሮች፡
- በልዑል አምላካችን አላህ ካልሆነ በስተቀር በሌላ መማል እንደማይፈቀድ፤
- ከላቀው አላህ ውጭ ባለ አካል መማል ከትንሹ ሺርክ መሆኑ
ስድስተኛው ሐዲሥ፡

መልስ - ከአነስ ኢብኑ ማሊክ አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ «ከአባቱ፣ ከልጁ እና ከመላው የሰው ልጆችም ሁሉ እርሱ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ የሆንኩት እኔ እስካልሆንኩለት ድረስ ማናችሁም ቢሆን አላመናችሁም።" ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
- ነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ከሰዎች ሁሉ በላይ ይበልጥ ተወዳጅ መሆን እንዳለባቸው፤
- እርሳቸውን ከማንም በላይ መውደዱም ከኢማን ምሉእነት እንደሆነ፤
ሰባተኛው ሐዲሥ

መልስ - ከአነስ ኢብኑ ማሊክ አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ «ማናችሁም ቢሆን ለራሱ የሚወደውን ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ ኢማኑ አልተሟላም።" ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- ማንኛውም አማኝ ለራሱ የሚወደውን ለሌሎች አማኞችም መውደድ እንዳለበት፤
- ያን ማድረጉም ከኢማን ሙሉነት እንደሆነ
ስምንተኛው ሐዲሥ

መልስ - ከአቢ ሰዒድ ረዲየሏሁ ዐንሁ በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ "ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ! (ሱረቱል ኢኽላስ) የቁርኣን አንድ ሶስተኛውን ታክላለች።" ቡኻሪይ ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- የሱረቱል ኢኽላስን በላጭነት
2- የቁርኣን አንድ ሶስተኛውን የሚታክል መሆኗ።
ዘጠነኛው ሐዲሥ፡

መልስ - ከአቢ ሙሳ ረዲየሏሁ ዓንሁ በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ “'ላ ሐውላ ወላ ቁወተን ኢላ ቢላህ' (ትርጉሙም: በአላህ ካልሆነ በቀር ምንም ኃይልም ሆነ ብልሀት የለም) ማለት ከጀነት ድልቦች መካከል አንዱ ነው።" ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- የዚህ ቃል ትሩፋት እና ከጀነት ድልቦችም አንዱ ስለመሆኑ፤
2- የትኛውም ባርያ በሀይሉም ይሁን በብልሀት ብቻ ከመተማመን ተቆጥቦ በአላህ ብቻ መደገፍ እንደሚገባው፤
* አስረኛው ሐዲሥ፡

መልስ - ከአን-ኑዕማን ቢን በሺር አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው እንደተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ብሏል፡- “አዋጅ! በሰውነት ውስጥ አንዳች ቁራጭ ስጋ አለች። ይህች ቁራጭ ስጋ ከተስተካከለች ሰውነት ሁሉ ይስተካከላል፤ እርሷ ከተበላሸች ደግሞ ሰውነት ሁሉ ይበላሻል።አዋጅ! እርሷም ልብ ነች።" ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- የልብ መስተካከል ውጭም ዉስጥም እንዲስተካከሉ ያደርጋል፤
2- ልብ እንዲስተካከል ትኩረት የመስጠት አስፈላጊነት፤ ምክንያቱም ሰውነት የሚስተካከለው በርሷው ነውና፤
* አስራ አንደኛው ሐዲሥ:

መልስ - ከሙዓዝ ኢብኑ ጀበል ረዲየሏሁ ዓንሁ በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ “ከዱኒያ የመሰናበቻ ቃሉ 'ላ ኢላሃ ኢለሏህ' የሆነ ሰው ጀነት ገባ።" አቡ ዳውድ ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- የ'ላ ኢላሃ ኢለሏህ' ትሩፋት፤ ማንኛውም ባርያ ጀነት የሚገባው በርሷው መሆኑ፤
2- ከዱኒያ የመሰናበቻ ቃሉ 'ላ ኢላሃ ኢለሏህ' የሆነ ሰው ያለው የላቀ ትሩፋት፤
* አስራ ሁለተኛው ሐዲሥ:

መልስ - ከዐብደላህ ኢብኑ መስዑድ ረዲየሏሁ ዓንሁ በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ “ሙእሚን ዘላፊ፤ ተራጋሚም አይደለም፤ ወይም ባለጌ አልያም ስድ አይደለም።" ቲርሚዚይ ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1 - ውሸት እና አስቀያሚ ንግግሮች ሁሉ የተከለከሉ ስለመሆናቸው፤
- ከዚህ መጠንቀቅም ሙእሚን በአንደበቱ የሚላበሰው ባህርይ ስለመሆኑ፤
* አስራ ሶስተኛው ሐዲሥ:

መልስ - ከአቡ ሁረይራ አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው በተላለፈ ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን እንዲህ ብለዋል፦ “የአንድ ሰው እስልምናው ያማረ ለመሆኑ ምልክቱ ከማይመለከተው ነገር መታቀቡ ነው።" ቲርሚዚይና ሌሎችም ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- ማንኛውም ሰው ለዲኑም ለዱኒያውም የማይመለከተውን (የማይጠቅመውን) ነገር መተው እንዳለበት፤
2- እንቶፈንቶ መተው ከእስልምና ማማር እንደሆነ
* አስራ አራተኛው ሐዲሥ:

መልስ - ከዐብደላህ ቢን መስዑድ በተላለፈ ሐዲሥ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡- “ከአላህ ኪታብ (ከቁርአን) አንዲት እንኳ ሐርፍ (ሆሄ) የቀራ ሰው በእርሷ ሐሰና (መልካምነት) ይመዘገብለታል። አንድ ሐሰና (መልካምነት) ደግሞ በአስር እጥፍ ነው የሚመነዳው። ይህን ስላችሁ 'አሊፍ ላም-ሚም' አንድ ሐርፍ ነው እያልኳችሁ አይደለም። 'አሊፍ' ራሱን የቻለ ሐርፍ ነው። 'ላም' ራሱን የቻለ ሐርፍ ነው። 'ሚም' ራሱን የቻለ ሐርፍ ነው።" ቲርሚዚይ ዘግበውታል።
ከሐዲሡ ከሚወሰዱ ቁምነገሮች መካከል፡
1- ቁርኣንን መቅራት ያለው ትሩፋት፤
2- በሚቀራው እያንዳንዱ ሐርፍ ሐሰና የሚመዘገብ ስለመሆኑ።